top of page
IMG_3621.jpeg

ታላቁ ተስፋ

"ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።"

​የሐዋሪያት ሥራ 1፥11

ተስፋና የሰው ምድራዊ ሕይወት በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው። ሰው ተስፋ ከሌለው የመኖር ፍላጐት ሊኖረው አይችልም። ለዚህ ነው ተስፋ መቁረጥ አንዱ የሰው ልጅ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የሚኖረው። ንጉሥ ዳዊት ስለ ተስፋ ሲናገር እንህ አለ፦ "ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች" (መዝሙር 16፥9)። ምንም ባይኖራትና ባይሆንላት እንኳን ሥጋችን የሚኖረው በተስፋ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥1-2 ላይ "ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና" በማለት ሥጋችን የሚናፍቀውን ተስፋ ይገልጠዋል።

ለምሳሌ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ያወጣበትን ተስፋ ስንመለከት "ከነዓንን አወርሳችኋለሁ" የሚል ነበር። ይህም ተስፋ ነበር የእስራኤልን ሕዝብ የመኖር አቅም የሰጣቸው። ይህ ተስፋ በደበዘዘባቸው ቁጥር ሕዝቡ የሚፈልጉት ወደ ግብጽ መመለስ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የመሢሁን ወደዚህ ምድር መምጣት በእምነት እያዩ ተስፋቸውን በእርሱ ላይ አድርገው ይኖሩ ነበር። የመሢሁ የመምጣቱ ተስፋ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ እንዲኖሩ ኃይልን ሰጥቶአቸው ነበር። "አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።" (ዩሐንስ 8፥56) በፊታቸው ካለው ተስፋ የተነሣ የኖሩት ኑሮ እጅግ የሚገርም ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ እንዲህ ሲል ይተርክልናል፦ "በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።" (ዕብራውያን 11፥37-38) ተስፋ እንዲህ ያለ ሕይወት የመኖር አቅም የሚሰጥ መሆኑን ይመሠክሩልናል።

በአዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛ ደግሞ የምንጠባበቀው ታላቁ ተስፋ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም የመምጣቱን የክብር ተስፋ ነው። ያ ቀን እንዴት ድንቅ ይሆን! ዓይኖቻቸው የበሩላቸው ሰዎች ከምድር ስኬት አልፈው የሰማዩን ተስፋ የሚጠባበቁ ናቸው። የእምነት አባቶች ዓይናቸውን ከምድራዊ ነገር ላይ አንስተው በዚህ ታላቅ ተስፋ ሲመላለሱ እንደ መጻተኛ ኖሩ። የዚህን ተስፋ እርግጠኛነት ተረድተን ብንመላለስ በሚነሱብን ፈተናዎች መደንገጥና መናወጥ አቁመን በድልነሺነት መንፈስ መመላለስ የዘወትር ሕይወታች ይሆናል። ዘማሪው በዘመኑ ሁሉ ስለተነሱበት ሰልፎች የነበረውን እይታ በመዝሙር 129፥1-2 ላይ ሲገልጠው እንዲህ አለ፦ "እስራኤል፦ ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ ይበል ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ፤ ነገር ግን አላሸነፉኝም።"

እንግዲህ እርስ በእርሳችን በዚህ ታላቅ ተስፋ ዛሬም እየተበረታታን የሚመጣውን ሙሽራችንን ኢየሱስን እንጠባበቅ! "እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።" (የሐዋሪያት ሥራ 1፥10-11)

ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን!

ፓስተር መስፍን ማሞ

7ቱ መመሪያዎች

ለመልካም ሕብረት

“ከክርስቶስ ጋር ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን፣ ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቊጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመ ውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።” (ፊልጵስዩስ 2፥1-4)

 1. ፍቅር - ፍቅር ከእኔነት ሕይወት ይገላግለናል። በፍቅር ውስጥ ራስ ወዳድነት ሥፍራ የለውም።

  • “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብት ዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዩሐንስ 13፥34-35)

 2. ማበረታታት - “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ።” (ኤፌሶን 4፥29)

  • ለማነጽ እንጂ ለመፍረድ አልተጠራንም።

  • አዎንታዊ ገጽታው የጎላ ግንኙነት ያስፈልገናል።

  • ግሳጼያችን በየውሃት መንፈስ ሊታጀብ ይገባል።

  • “ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል።” (ገላትያ 6፥1)

  • “እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።” (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥11)

 3. መከባበር - “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” (ሮሜ 12፥10)

  • “ሁሉን አክብሩ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥17)

 4. ኃላፊነትን መውሰድ - “አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” (ሉቃስ 6፥42)

  • ሌላውን ለመገሰጽ ኃላፊነት ልንወስድ እንደሚገባን ሁሉ፥ እኛም ለገዛ ስኅተቶቻችን ኃላፊነት ለመውሰድ የበሰልን ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል።

 5. ራስን መግዛት - “መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ።” (ኤፌሶን 4፥31)

 6. ይቅርታ - “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።” (ኤፌሶን 4፥32)

 7. ጸሎት - “ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል።” (ያዕቆብ 5፥16)

  • “ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ።” (ማቴዎስ 5፥43-44)

ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን!

ፓስተር መስፍን ማሞ

bottom of page